በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው ከነበሩ ግጭቶች ጀርባ የአሸባሪው ሕወሓት እጅ መኖሩ በምርመራ ተረጋግጧል

ሰኔ 14, 2022
ግጭቶች ጀርባ የአሸባሪው ሕወሓት እጅ እንዳለበት በምርመራ መረጋገጡን ፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ። በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የግጭትና አለመረጋጋት ክስተቶች መስተዋላቸው ይታወቃል። በተለያዩ ምክንያቶች በተከሰቱት ግጭቶች የበርካታ ወገኖች ህይወት ሲያልፍ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀልም ተከስቷል። በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ተሳታፊ የነበሩ አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ፍትህ እንዲያገኙ መሰራቱን ፍትህ ሚኒስቴር ገልጿል። የፍትህ ሚኒስትር ደኤታ ፍቃዱ ጸጋ፤ በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶችን መንስኤ ለማጣራትና ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በተደረገው ምርመራ የአሸባሪው ህወሃት የጥፋት እጆች መኖራቸው ተረጋግጧል ብለዋል። አሸባሪው ሕወሓት ግጭቶችን በጦር መሳሪያና በበጀት በመደገፍ እንዲሁም ስምሪት በመስጠት ስለመሳተፉ በመረጃና ማስረጃ ተረጋግጧል ብለዋል። ”እኔ ያልመራኋት አገር መቀጠል የለባትም” ብሎ የተነሳው አሸባሪ ቡድን አገር ለማፈራረስ የተለያዩ የጥፋት አማራጮችን መጠቀሙን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። የፍትህ ሚኒስቴር ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በቴፒ፣ በቡራዩና በአዲስ አበባ፣ በአሶሳ እና ሌሎችም አካባቢዎች የተፈፀሙ ወንጀሎች ተጣርተውና ምርመራ ተደርጎ ውሳኔ እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል። በጌዲዮና ጉጂ እንዲሁም በሀዋሳ በተፈጠሩ ግጭቶች የወንጀሉ ተሳታፊ የነበሩ አካላትም የፍርድ ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል። መነሻቸውን የሀይማኖትና የወሰን ጉዳይ አድርገው በቅርቡ የተከሰቱ ወንጀሎችን የሚመረምር ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን ጠቅሰዋል። በጎንደር፣ በደባርቅና በወራቤ ሀይማኖትን ሽፋን ያደረጉ እንዲሁም በጂንካና ደራሼ ወሰንን መነሻ አድርገው የተከሰቱ ግጭቶችን በማጣራት ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ሀይማኖትንና ብሔርን መነሻ አድርገው የተከሰቱ ግጭቶች በፌዴራል መንግስት ብቻ እንዲታዩ መወሰኑንም ተናግረዋል። ለፍትህ ተደራሽነት ከመስራት በተጓዳኝ በባህላዊ እሴቶች የእርቅ ተግባራት እንዲከናወኑ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በቀጣይም የድንበርና የወሰን ጉዳዮችን በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት ይሰራል ብለዋል። የጥፋት ሃይሎች አገር የማፍረስ እንቅስቃሴ አሁንም የቀጠለ ቢሆንም መንግስት ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረግና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ አጠናክሮ ቀጥሏል።
https://aapp.gov.et/wp-content/uploads/2022/06/LOGO-w.png

© 2023 Copyright Addis Ababa Prosperity Party

አግኙን
0116674406
P.O.Box: 1352
303781
Total Visitors