July 23, 2023

1, “በአዲስ አበባ ፕሮጀክት መጀመር ብቻ ሳይሆን በጊዜ ማጠናቀቅ የሚያስችል የስራና የአሰራር ባህል ተፈጥሯል!!”
– የከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክት
“ከ200 በላይ ለሚሆኑ የኢትዮጵያ ከተሞች ከንቲባዎች በአዲስ አበባ ከለውጡ ወዲህ አቅደን በመፈፀም ያስገኘናቸዉን ስኬቶችንና ዉጤታችንን ያሳዩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እንዲሁም ሰው ተኮር ስራዎቻችንን አስጎብኝተናቸዋል።
በመቀጠልም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የበለፀጉ ከተሞችን ለመፍጠር ከንቲባዎች በሚጫወቱት ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገን ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ተቀብለናል።
በአዲስ አበባ ሜጋ ፕሮጀክቶች ገንብታ የከተማዋ ገጽታ ተቀይሮ የቱሪስት መዳረሽ ሆናለች ፣ በአዲስ አበባ ፕሮጀክት መጀመር ብቻ ሳይሆን በጊዜ ማጠናቀቅ የሚያስችል የስራና የአሰራር ባህል ተፈጥሯል ፣ በአዲስ አበባ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች አለሁ የሚል አሳቢ አመራርም ተፈጥሯል::
የኢትዮጵያ ከተሞች ከንቲባዎች ከዚህ ስኬት ልምድ ወስደው ከተሞቻቸውን የማላቅ እና የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና የሚያቀሉ ሰው ተኮር ስራዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተስፋ አደርጋለሁ።”

2፣ የአዲስ አበባ መምህራንና የዘርፉ አመራሮች በመዲናዋ የተገነቡ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራንና የትምህርት አመራሮች በመዲናዋ
የተገነቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
መምህራኑ በለሚ ኩራ ክ/ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘውን የገበያ ማዕከል፣ መገናኛ አከባቢ በመገንባት ላይ ያለውን የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል እንዲሁም አብርሆት ቤተ መጻሕፍት እና ወዳጅነት ፓርክን ጎብኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አሊ ከማል÷ጉብኝቱ በዋናነት መምህራን በሀገር ግንባታ ሒደቱ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።
የመዲናዋ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ድንቅአለም ቶሌሳ በበኩላቸው ÷መምህራን ያፈሯቸው ባለሙያዎች ከፍተኛ ፕሮጀክቶችን ገንብተው በመመልከታቸው ደስተኛ እንደሆኑ መናገራቸውን የቢሮው መረጃ ያመላክታል።

3; “የብልፅግና ጉዟችን በጽንፈኞች እና በሰው ገዳዮች አይደናቀፍም!!”
– የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በነበሩት የአቶ ግርማ የሺጥላ የአስከሬን ሽኝት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ እንደተናገሩት አቶ ግርማ የሺጥላ ሰው ወዳድ ተግባቢና ቅን ስብዕናን የተላበሰ መሪ ነበር ብለዋል።
አቶ ግርማ ሀገራዊ ራዕይን የተረዳ በሳል መሪ ነበር ያሉት አቶ አደም ፋራህ የአማራ ህዝብ መብትና ጥቅም የሚከበርበትን በሚገባ የተገነዘበ በኢትጵያዊያ ዘረኝነትንና ፅንፈኝነትን የሚፀየፍ እውነተኛ የብልፅግና አመራር እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
የብልፅግና ጉዟችን በጽንፈኞች እና በሰው ገዳዮች አይደናቀፍም ያሉት አቶ አደም የህዝብን መሪ እየገደሉና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራዊያዊ መብቶች እየገፈፉ ሊሳካ የሚችል አንዳችም አላማ አይኖርም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ስርዓት አልበኝነት የከፋ ዋጋ እንደሚያስከፍልና ጽንፈኞችን ስርዓት ለማስያዝ በሚደረገው ሂደት ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን እንዲቆም አቶ አደም ጥሪ አቅርበዋል፡፡  · “ግርማ ሕዝብን ለማገልገል ድንበር የማያውቅ መሪ ነበር”
– ከንቲባ አዳነች አቤቤ
የአቶ ግርማ የሽጥላ አሰከሬን ሽኝት በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ እየተካሄደ ነው፡፡ ክብራቸውን እና የሕዝብ
አገልጋይነታቸውን በሚመጥን መልኩ እየተካሄደ በሚገኘው የሽኝት መርሐ ግብር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የግርማን ሞት መሥማት አብረናቸው ለሰራነው ለእኛ አሳዛኝም፤ አስደንጋጭም ነበር ያሉት ከንቲባዋ ግርማ የማይሞት ዓላማ ያነገቡ መሪ ናቸው ብለዋል፡፡ ግርማ ዕድለኛ ነው ላመነበት እውነት ሕይዎቱን አሳልፎ እስከመስጠትም ደርሷል ብለዋል፡፡
ሞት ሥጋን እንጂ ዓላማን አይገድልም ያሉት ከንቲባዋ ግርማ ማስመሰል አይችልም፣ ለእውነት ኖሯል ስለእውነትም አልፏል ነው ያሉት፡፡ “ግርማ ሕዝብን ለማገልገል ድንበር የማያውቅ መሪ ነበር” ያሉት ከንቲባዋ ግርማ የሕዝቦች ወንድማማችነት እና የኢትዮጵያ አንድነት የሚያስጨንቀው መሪ ነበርም ብለዋል፡፡ ግርማ ዘመኑን ሁሉ ቤተሰቡን ትቶ ሕዝብን ለማገልገል ሰርቷል ያሉት ከንቲባ አዳነች ቤተሰቦቹን መንከባከብ አሁን ባለው የግርማ የትግል ወንድሞች ትከሻ ላይ ያረፈ ነው ብለዋል፡፡
የአቶ ግርማ የሺጥላ አስከሬን በወዳጅነት አደባባይ ሽኝት እየተደረገለት ይገኛል።የአቶ ግርማ የሺጥላ አስከሬን በአሁኑ ሰዓት በማርሽ ቡድን፣ በወዳጅ ዘመዶቻቸው እና በስራ ባልደረቦቻቸው ታጅቦ ወዳጅነት አደባባይ ደርሷል።
በወዳጅነት አደባባይም የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንቶች አቶ ደመቀ መኮንን እና አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ፣ የአቶ ግርማ የሺጥላ ባልደረቦች ፣ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች አሸኛኘት ያደርጋሉ።
በመቀጠልም የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በወላጆቻቸው ፍላጎት እና ጥያቄ መሰረት በተወለዱበት ሰሜን ሸዋ ዞን መሀል ሜዳ እንደሚፈጸም ተገልጿል።
“ዕንቅፋትና ፈተናዎቻችን አሰናክለው አያስቀሩንም፤ እንዲያውም የመሸጋገሪያ ድልድዮች ሆነው ያገለግሉናል። ዓለማችን ላይ ቁልፍ ግኝቶች የተገኙት፣ አስደማሚ ቴክኖሎጂዎች የተሠሩትና ችግር ፈቺ መፍትሔዎች የተፈጠሩት በፈተና ጊዜ ነው። በፈተና ጊዜ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዕንቅፋትን ወደ ዕድል ለመለወጥ በሚነሡ ብርቱዎች ትጋት እንደሆነ የብዙ ሀገራት የሥልጣኔ ታሪክ ያስተምረናል።”
– ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ

https://aapp.gov.et/wp-content/uploads/2022/06/LOGO-w.png

© 2023 Copyright Addis Ababa Prosperity Party

Contact
0116674406
P.O.Box: 1352
299123
Total Visitors