ፈተናዎችን በድል ተሻግረን ስኬቶቻችንን እናፀናለን !!

July 10, 2023

ኢትዮጵያ ከድህነት ወደ ብልፅግና ተስፋ ሰጪ ጉዞ ጀምራ በዜጎቿ የጋር ህብረት ወደ ፊት እየገሰገሰች ትገኛለች። ጉዞው ሁለንተናዊ ብልፅግናን እውን ለማድረግና የዜጎችን ተጠቃሚነት በየደረጃው የማረጋገጥ ሰፊ ራዕይን ያካተተ ሲሆን ባለፉት አምስት ዓመታት የተካሄደው የለውጥ እንቅስቃሴ በብዙ ስኬቶች የታጀበና እና ብዙ ፈተናዎችን ያሳለፈ ነበር።

እነዚህ ፈታኝ ስኬቶች ኢትዮጵያን ለውጭና ውስጣዊ ፈተናዎች ሳትንበረከክ ወደፊት ለመራመድ ትልቅ አቅም ያላት ሀገር እንድትሆን ያስቻሏት እና ማንኛውንም ፈተና ወደ ዕድል በመቀየር የዜጎቿን የልማት ፍላጎትና ብልጽግና ለማሟላት የምትተጋ ሀገር መሆኗን አስመስክሯል።

የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጀመረው ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ በተግዳሮቶች ሳይደናቀፍ፣ እንቅፋቶችን ሁሉ ወደ መልካም ዕድል በመቀየርና የታለመለትን ግብ ለማሳካት እየተጓዘ ነው።

ሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲን የሚያጎለብት፣ እኩልነትን የሚያረጋግጥ፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባትና ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነት የሚያጠናክር በማከናወን በለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች። በዚህ የለውጥ መንገድ እያንዳንዱ ዜጋ የሚተማመንባት ጠንካራና የተከበረች ሀገር ለመፍጠር ረጅም መንገድ መሄድ ያስፈልጋል።

ስለሆነም የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ወደ እድሎች በመቀየር የዜጎች እኩልነትን፣ ህብረብሄራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ እና ጠንካራ ዲሞክራሲ የሰፈነባትና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን በመረዳት ስኬቶቻችንን ማፅናትና በጋራ መተባበር አለብን።

ከአኩሪ ታሪኮቻችን ለቀጣይ ጉዟችን ተሞክሮ ሰንቀን፤ ከችግሮች ተምረን፣ ጥፋቶችን አርመን ወደ ፊት እንገስግስ !!

የብሔር፣ የባህል፣ የሀይማኖት እና መሰል ብዝሃነቶች የውበታችንና የጥንካሬያችን ምንጭ ናቸው። እነዚህ ብዝሀነቶች ተከብረው ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን የበለጠ እንዲጠናከር ለውጡ በከፈተው የዲሞክራሲ በር የሀሳብ ብዝሃነቶችን በአግባቡ ለማስተናገድ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ይደረጋሉ፣ እየተደረጉም ነው።

በመደማመጥ፣ በመሰማማት፣ ራስን በሌላው ቦታ አድርጎ በማየት፣ ላለመግባባት ሳይሆን ለመግባባት በመወያየት፣ የግልን ወይም የቡድንን ፍላጎት ሳይሆን ህብረ ብሔራዊነትን ታሳቢ በማድረግ የሀሳብ ብዝሀነትን ማስተናገድ ለምንገነባው ጠንካራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ወሳኝ ነው።

ብሔራዊ መግባባት፣ ብሔራዊ የሽግግር ፍትህ እና ሌሎችም ሁሉን አካታች ጥረቶችም ህብረብሔራዊ አንድነታችንን የሚያጠብቁ በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው በእርግጥም ኢትዮጵያውያንን ወደ ተሻለ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ናቸው።

ተግባራዊ ለማድረግ የታሰበው ብሔራዊ የሽግግር ፍትህ አገራችን ጦርነት ውስጥ በነበረችባቸው ወቅቶች በዜጎች ላይ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመለየት ለታሪካዊ ቁርሾ እንዳይዳርጉን እልባት ለመስጠት ከመደበኛው የፍርድ ቤት ተግባር በተጨማሪ የጎላ ጥቅም እንደሚያስገኝ እምነት ተጥሎበታል።

የሽግግር ፍትህ ረቂቅ ፖሊሲ ወደ ተግባር ሲገባ ተጠያቂነትንና ይቅር መባባልን አንድ እርምጃ በማራመድ እየተገነባ ላለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ለህግ የበላይነት መከበር እና ለብሔራዊ መግባባታችን መጎልበትም ምቹ መደላድል ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል።

የፓርቲያችን አመራር፣ አባል፣ ደጋፊ እና አጠቃላይ ህዝባችን በዚህ ወሳኝ ወቅት በተሰማራበት ሁሉ ታሪካዊ አሻራችንን ከማሳረፍ በተጨማሪ የሀገራችን የብልፅግና ጉዞ ለማደናቀፍ ለሚጥሩና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለማንም የማይበጁ ከፋፋይ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ አካላትን መመከትና ማረም ከሁላችንም ይጠበቃል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን አኩሪ ታሪኮች ለቀጣይ ጉዟችን ተሞክሮ ሰንቀን፣ ከችግሮች ተምረን፣ ጥፋቶችን አርመን ወደ ፊት ለመገስገስ በዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ለኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና መሰረት የሚሆኑ ለትውልድ ተሻጋሪ ተግባራትን በሀገራዊ ስሜት መከወን ይገባል።

https://aapp.gov.et/wp-content/uploads/2022/06/LOGO-w.png

© 2023 Copyright Addis Ababa Prosperity Party

Contact
0116674406
P.O.Box: 1352
304054
Total Visitors